Skip to main content
x

ክቡር ሚኒስትሩ ልብሳቸውን ቀይረው ኤርፖርት ሲሄዱ ባለሀብቱን ለመቀበል አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞችና ባለሀብቶች ተሰብስበው አገኙ፡፡ ከጋዜጠኛው ጋር እያወሩ ነው

• ብዙ ሰው ሊቀበላቸው መጥቷል አይደል እንዴ? • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡ • ይኼ ሁሉ ሰው ግን እንዴት መጣ? • ባለሀብቱ እኮ ብዙ ወዳጆች አሏቸው፡፡ • አንተም ወዳጃቸው ነህ? • እኔማ በዚሁ ለመወዳጀት አስቤ ነው፡፡ • ይኼ ሁሉ ሰው እንደሚኖር አላወቅኩም ነበር፡፡ • አብዛኛው ሰው እኮ ሊያስጨርስ ነው የሚመጣው፡፡ • ምንድነው የሚያስጨርሰው? • የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች ነዋ፡፡ • ያልከኝ አልገባኝም፡፡ • እዛ ጋ ያለውን ባለሀብት አዩት? • አዎን፡፡ • እሱ የጀመረውን ሕንፃ እንዲጨርሱለት ነው የመጣው፡፡ • እሺ፡፡ • እዛ ጋ ያለውን አርቲስት አዩት ደግሞ? • አዎን፡፡ • እሱ ደግሞ የጀመረውን ቤት ሊያስጨርስ ነው የመጣው፡፡ • አንተስ ምን ልታስጨርስ ነው? • ዕቁቤን!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ይደውልላቸዋል

• ክቡር ሚኒስትር ሰሙ አይደል? • ምኑን? • ፌስቡክ ላይ የሚወራውን አልሰሙም እንዴ? • እኔ እኮ ፌስቡክን ስም አውጥቼለታለሁ፡፡ • ምን ብለው? • ፌክቡክ፡፡ • ለምን? • እንዴ ፌስቡክ እኮ የአደገኛ ቦዘኔዎች መፈንጫ ሠፈር ነው፡፡ • እንዴት ክቡር ሚኒስትር? • ስማ እዛ የሚወራው ወሬ ፌክ ነው፣ ሰዎቹም ፌክ ናቸው፡፡ • መረጃ ታዲያ ከየት ነው የሚያገኙት ክቡር ሚኒስትር? • እሱን ለእኛ ተወው፡፡ • ከየት ነው የሚያገኙት? • ከተለያዩ የመረጃና ደኅንነት ምንጮቻችን አሊያም ከታወቁ ሚዲያዎች መረጃ እናገኛለን፡፡ • ስለዚህ ፌስቡክ አይሆንም እያሉ ነው? • ነገርኩህ እኮ እሱ ፌክቡክ ነው፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ብሎገር ጋ ደወሉ

• የበሬ ወለደ ጽሐፎች ያን ያህል ተቀባይነት እያገኙ አይደለም፡፡ • ስማ የምትጽፈው ጽሑፍ እውነት እንዲመስል የሚያደርጉ ሰዎችንም መልምለሃል አይደል? • እሱማ መልምያለሁ ግን ትንሽ የበጀት ጭማሪ ያስፈልገኛል፡፡ • ተጨማሪ በጀት መንግሥት ራሱ መከልከሉን አልሰማህም እንዴ? • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር ወድጄ አይደለም? • ምንድነው የምታወራው ሰውዬ? • የጫት ወጪዬ ከአቅሜ በላይ ሆኖብኝ ነው፡፡ • እና የጫት እርሻ ይገዛልህ? • ከተቻለማ ደስ ይለኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡ • ቀልዱን ትተህ ሥራህን በአግባቡ ሥራ፡፡

ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር ውጭ አገር ቢዝነስ የሚሠራ ወዳጃቸው ደወለላቸው

የት ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር? አገሬ ነዋ። አሁን እንደው አፍ ሞልቶ አገር አለ ማለት ይቻላል? ምን እያልክ? ደግሞ ምን ተፈጠረ? ይኸው በየቀኑ የምንሰማው እልቂት፣ መፈናቀል፣ ግጭትና ረብሻ አይደል እንዴ? እባክህ ይኼ የፀረ ሰላም ኃይሎች ወሬ ነው። እና አገር ሰላም ነው እያሉኝ ነው? ሰላም ቢሉህ ሰላም ነው እንዴ? ኧረ ተው ክቡር ሚኒስትር። እውነቴን ነው የምልህ፤ ሰሞኑን ራሱ ከአንድ ሥራ ያገኘሁት ትርፍ ቀላል እንዳይመስልህ? ከምንድን ነው ትርፍ ያገኙት? ከዶላር ጭማሪው። እውነት? በቃ የጀመርኩትን ሕንፃ የሚያስጨርሰኝ ነው ስልህ? ግብር ከፈሉ ታዲያ? የምን ግብር? ይኼን ንፋስ አመጣሽ ታክስ ምናምን የሚሉትን ነዋ። ንፋሱን ያመጣሁት እኔ አይደለሁ እንዴ? ለነገሩ እርስዎ እንኳን ንፋስ አውሎ ንፋስ ማስነሳት ይችላሉ።

የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር በጠዋት ከቤት ሊወስዳቸው መጣ

ክቡር ሚኒስትር የሚያሳዝነኝ መጥፎ መሆናችሁ አይደለም፡፡ ምን እያልክ ነው? አሪፍ መጥፎ እንኳን አይደላችሁም፡፡ ምን ይዘባርቃል ይኼ? ለማንኛውም ያኔ ትግል እንዴት ነበር የገቡት? ምን እያልከኝ ነው? ማለቴ ለመታገል ያነሳሳዎት ምንድን ነበር? ያው ሕዝቡ ተበድሏል፡፡ ተጨቁኗል ብዬ አስብ ነበር፡፡ እሱ ነበር ምክንያትዎ? በወቅቱ የነበረው መንግሥት አፋኝና ጨቋኝ ስለነበር ያንን ሥርዓት ለመጣል ነው የታገልኩት፡፡ ስለዚህ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ እያሉኝ ነው? ወዴት ልትሄድ ነው ደግሞ? እኔም ልታገል ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት

ለእያንዳንዱ ተሳታፊ ኮፍያና ቲሸርት መዘጋጀት አለበት፡፡ መቼ ጨረታ ልናወጣ? ጊዜ ስለሌለ እሱን ለእኔ ተወው፡፡ አያስጠይቀንም ክቡር ሚኒስትር? ትልቅ እንግዳ እኮ ነው የሚመጣው? ለመሆኑ በቲሸርትና በኮፍያው ላይ ምንድነው የሚጻፈው? እንኳን ለአገርህ አበቃህ፡፡ እንግዳው ኢትዮጵያዊ ነው እንዴ? እህሳ? ይኼን ያህል ክብር የተሰጠው እንግዳ ማን ነው? ስኳሩ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከግምገማው እንደወጡ ለደላላ ወዳጃቸው ደወሉ

ክቡር ሚኒስትር ከቦታዎ ከመነሳትዎ በፊት ጥሩ ስትራቴጂ መቀየስ አለብን፡፡ የምን ስትራቴጂ? እርስዎን ማቋቋም አለብን፡፡፡ ለነገሩ ከመንግሥት የተማርኩት ጥሩ የማቋቋሚያ ሥልት አለኝ፡፡ ምን ዓይነት ሥልት ክቡር ሚኒስትር? ከባለሀብቶች ገቢ ማሰባሰብ ነዋ፡፡ ቴሌቶን ልናዘጋጅ? ገንዘቡን የምናሰባስበው በቴሌቶን አይደለም፡፡ ታዲያ በምንድነው? በኤስኤምኤስ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር በስልክ እያወሩ ነው

ሙስና የግል ሴክተሩም እንደሚነካ መቼም ታውቂያለሽ፡፡ እኔን አይመለከተኝም አልኩህ፡፡ አሁን ደግሞ ዋና ትኩረትቸው በባለሥልጣናት ዙሪያ ያሉ ሰዎች ላይ ነው፡፡ እያስፈራራኸኝ ነው? ለማንኛውም ወደ ዱባይ ብትሄጂ ጥሩ ነው፡፡ ስማ እኔ የመጣብኝን እቀበላለሁ፡፡ እስርም ቢሆን? ለምን እታሰራለሁ? ያልተገባ ሀብት አካብተሻል ተብለሽ ነዋ፡፡ በቃ እንደሌሎቹ በስሜ ያለን ሀብት ሸጣችሁ ውሰዱት ብሎ መገላገል ነዋ፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ተመራማሪ ከሆነ የቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኙ

• ክቡር ሚኒስትር አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት? • ይቻላል፡፡ • በዓለም ላይ እንደ ኢሕአዴግ ሥልጠና የሚወድ ድርጅት አለ? • እየቀለድክ ነው? • እውነቴን ነው እንጂ ከዓመት ዓመት ሥልጠና ላይ ናችሁ እኮ? • ሕዝቡን ለማገልገል ሥልጠና ወሳኝ ነው፡፡ • በእርግጥ ሕዝቡን ለማገልገል ነው ሥልጠና የምትቀመጡት? • ታዲያ ለምንድነው? • ለአበል ነዋ፡፡